ቁርዓንን በሁሉም ቤት!!
🔹🔹🔹🔹🔹🔹
ጋዜጣዊ መግለጫ~~~
ኑር የቁርዓን ባንክ ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 500ሺ ቁርኣኖችን የማሰባሰብ መርሃግብር ማስጀመርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ የካቲት 15/2015 ተካሄድዋል፡፡
———————————
ሙሉ መግለጫው
ቢስሚላሂ አራህማን አልረሂም
ኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር የተሰጠ መግለጫ ።
እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ከሚያከናውናቸው በርካታ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መሐከል አንዱ ለኢስላማዊ ጀመአዎችና የበጎ አድራጎት ማህበራት በምክር ቤቱ ግምገማ መሰረት ህጋዊ አሰራርን ለሚከተሉ ማህበራት ፍቃድና እውቅና መስጠት መሆኑ ይታወቃል ።
በዚህ መሰረት ለኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር በቀን 28/02/2015 ዓ.ል የማህበሩን የዓመታት የስራ እንቅስቃሴን በመገምገምና የቀጣይ ዓመት ኘሮጀክቶቹን በመደገፍ ከምክር ቤቱ ህጋዊ እውቅና ድጋፍ ማግኘት ችሏል ።
ኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር የተመሰረተበት ዋነኛ ዓላማ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫዎች የሚገኙ መሳጂዶች ሐሪማዎች ዛዊያዎችና መድረሳዎች የቁርኣን ኮፒዎች እጥረትን ለመቅረፍ ሲሆን
ከተመሰረተበት ግዜ አንስቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ70 በላይ ከተማዎችና ከ143 በላይ የገጠር መንደሮች ማዳረስ ተችሏል
በዚህም መሰረት
:- ከ127 በላይ መድረሳዎች
:- ወደ 216 ለሚጠጉ መስጂዶች
:- ከ21 በላይ ትልልቅ ሀሪማና ዛውያዎች እንዲሁም በአራቱም አቅጣጫ ባሉ ፍፁም በረሃማና ለኑሮ አስቸጋሪ በሆኑ መንደሮች ውስጥ ለሚገኙ የቁርአን የማስተማሪያ ቦታዎች በጥቅሉ 165,237 በላይ የቁርኣን ኮፒዎችን ማሰራጨት የቻለ ሲሆን በአካል ያልደረስንባቸው ቦታዎች ደግሞ በደብዳቤ ተጠይቀን በተወካያቸው አማካኝነት ቁርኣኖችን ለመላክ ችለናል።
ማህበራችን ኑር የቁርኣን ባንክ ሙሉ በሙሉ ከበጎ ፍቃደኛ ግለሰቦች ከተለያዩ አህለል ኸይሮችና ከሚታወቁ ኢስላማዊ ተቋማትና ጀመአዎች እንዲሁም ባህር ማዶ ከሚገኙ እስላማዊ ጀመዓዎችና ግለሰቦች ቁርኣኖችን በማሰባሰብ ከብዙ ክፍለ ሀገራት የሚመጡ የቁርኣን ጥያቄዎችን የቀረፈ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የሚወድሙ የቁርኣን ኮፒዎችን ቦታው ድረስ ተጉዞ የመተካት ስራ በመስራት በሀገሪቱ በተወሰነ ደረጃ የቁርኣን እጥረትን ለመቅረፍ ችሏል።
ይህን መነሻ በማድረግና ማህበሩ በተለያዩ ጊዜያት በመላው ኢትዮጵያ የገጠር መንደሮች ውስጥ ባደረገው ጥናት መሰረት በዘንድሮ የረመዳን ወር የቁርኣን እጥረቱን ለመቅረፍ 500ሺ የቁርኣን ኮፒዎችን ከመዲናችን ከአዲስ አበባ ከተማና ከአጎራባች ከተሞች ከሙስሊሙ የማህበረሰብ ክፍል በማሰባሰብ በመላው ኢትዮጵያ ለማሰራጨት ሰፊ እቅድ ዪዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሲያበስር ከመላው ሙስሊም ህብረተሰብ ጋር ማሳካት እንደሚችል ሙሉ ለሙሉ በመተማመን ነው።
እንደሚታወቀው ታላቁ የረመዳን ወር የቁርኣን ወር እንደመሆኑ በሀገራችን በተፈጥሮና በሰውሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ የተቃጠሉና የወደሙ የቁርኣን ኮፒዎችን በመተካት ሙስሊሞች በቁርኣን ወር የቁርኣን እጥረት እንዳያጋጥማቸው ማድረግ የሁላችንም ሀላፊነት ነው።
በመሆኑም መላው የአዲስ አበባ ሙስሊም ነዋሪዎች እንዲሁም በአጎራባች ከተሞች ውስጥ የምትገኙ ሙስሊም ወገኖቻችን በዚህ ሰፊ ምንዳ በሚያስገኘው ተግባር ላይ በመሳተፍ የሁለት ዓለም ምንዳ ተካፋይ ትሆኑ ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን ።
ኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ያህል የሚቆይ ቁርኣን የማሰባሰብ መርሃግብር በከተማችን የሚገኙ መስጂዶች ያዘጋጀን ሲሆን ሙስሊሞች ከ1ጁዝ ጀምሮ እስከ 30 ጁዝ ቁርአኖችን አቅማችሁ በፈቀደ መልኩ በአቅራቢያችሁ በሚገኙ መሳጂዶች በመሄድ ለኑር ቁርአን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር ብላችሁ እንድትሰጡ እየጠየቅን ከአዲስ አበባ ውጪ ያላችሁ እና በዚህ ኘሮጀክት ላይ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ማድረግ ለምትፈልጉ በሙሉ በማህበሩ ህጋዊ ባንክ አካውንት በኩል በነየታችሁት የሙስሀፍ ቁጥር ልክ ገቢ ማድረግ የምትችሉ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን ።
በዚህ መርሃ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ሙስሊም ነዋሪዎች ፣ ተማሪዎች ፣ ሰራተኞች ህፃናትና ወላጆች እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራትና ዕድሮች በተጨማሪም ተቋማቶችና የንግዱ የማህበረሰብ ክፍል በሙሉ አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ኒያችሁን በማሳመር ለዚህ የበጎ ምንዳ ጥሪ ምላሽ በመስጠት መርሃ ግብሩን በመከታተል አዲስ አበባ በሚገኘው በኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር ዋና ቢሮ ፒያሳ ሶማሌተራ የገበያ ማዕከል 8ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 830 ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በጊዜያዊነት በተዘጋጁ ቢሮ በአካል በመገኘት ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደምትችሉ እየገለፅን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተመረጡ መስጂዶች ዘወትር በ5 ወቅት ሶላቶች ግዜ በመስጂዱ ውስጥ ለሚገኙ ኻዲሞች ቁርኣኖችን መስጠት የምትችሉ መሆኑን በድጋሚ እየገለፅን ባህር ማዶ ያላችሁ ሙስሊም ወገኖችም የዚህ ኸይር ስራ ምንዳ ተቋዳሽ እንድትሆኑ በአላህ ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን ።
በመጨረሻም ስለ ኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትም ሆነ ይህንን መርሃ ግብር ለማስተባበር የምትሹ የከተማችን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በአብሮነት ዘላቂ ስራዎችን ጭምር በጋራ ለመስራት እነዚህን አድራሻዎች በመጠቀም የማህበሩን አመራሮች በቀጥታ ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን ።
ቁርኣን ለሁሉም !
ሁላችንም በአንድነት ከተባበርን’ና የሚጠበቅብን ሃላፊነት ከተወጣን ኢንሻአላህ በመጪው የቁርኣን ወር በሀገሪቱ የትኛውም አካባቢ ለሚኖሩ ወገኖቻችን የቁርኣን እጥረት አያጋጥማቸውም ።
ኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ጋር በመተባበር ።
የካቲት 15 – 2015 ዓ.ል
አዲስ አበባ