ዳቡስ_አትንባቆ
ወቅቱ የሌሊት ነው ሰአቱ 9:30 ። ከታች በምስሉ የምትመለኩት የሂላል መስጂድ ቅጥር ግቢ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ዞን ዳቡስ አትንባቆ ቀበሌ ውስጥ ተገኝተናል ።
ከቦታው እንደደረስን ውዱእ ለማድረግ ውሃ መፈለግ ጀመርን ። ‘በቂ የሚባል ባይሆንም እንግዶች ስለሆናችሁ ለእናንተ ብለን ከሩቅ ቦታ ያመጣናት ውሃ አለች’ ብለው ጥቂት የውዱእ ውሃ ሰጡን ። እግረ መንገድ አካባቢው ላይ የውሃ እጥረት እንዳለ ሲያወጉን ቆይተው ለመፍትሔው የምትሰሩ ከሆነ ለአንድ የጉድጓድ ውሃ ማስቆፈሪያ አንድ መቶ ሀምሳ ሺ ብር ነው ሲሉ አስገረሙን ። ነገሩ እንዲያ ከሆነ በኛ በኩል አህለል ኸይሮች እንፈልጋለን አብሽሩ ብለን ወደ መስጂድ ውስጥ ዘለቅን ።
መስጂዱ በአካባቢው ሰዎች መዋጮ እንደነገሩ የተሰራ ሲሆን በእርግጥም እድሳት ይፈልጋል ። ውስጡም ጨለማ የወረሰው ሲሆን በመስኮቱ ከሚገባ ጥቂት የብርሃን ጭላንጭል በተጨማሪ እጅግ ትንሿ አንድ ፍሬ የሶላር አምፖል ጥቂት ብርሃን ትተፋለች ። ብዙ አልቆየም የአዛን ጥሪ ተሰማ ። የሱብሂ ሰላት ነው ። ያውም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ። ግን በደቂቃዎች ውስጥ የሰላት ሶፉ መውላት ጀመረ ። በርካታ የአካባቢው ህፃናት ከሞቀ ጎጇቸው ይልቅ የመስጂዱን ብርድ ወደው ከሌሊት እንቅልፍ በተሻለ የጀመአ ሰላትን መርጠው ከመስጂዱ ቅጥር ከትመዋል ። መስጂዱ በሰጋጆች ለሙሉነት የቀረበ ቢሆንም በቂ የድምፅ ማጉያ ካለመኖሩ ጋር ሁሌም ኢማሙን ተከትሎ ድምፅ የሚያስተጋባ ሰጋጅ አለ በእርሱ ድምፅ ተመርተን ሶላታችንን አገባደድን ።
የሱብሂ ሶላት እንደተጠናቀቀ ድንገት ህፃናቱ ይሮጡ ጀመር! በአግራሞት ተከተልናቸው ። ታዳጊዎቹ ቁርኣንን እየፃፉ የሚቀሩበትን ‘ሉህ’ (ጣውላ ላይ የተፃፈ ቁርኣናቸውን) ይዘው ወደ መስጂዱ ግቢ ጎረፉ ። እኛም በሁኔታው ግር እየተሰኘን ከአቅሪያቸው ጋር በመሆን ህፃናቱ አጠገብ አረፍ አልን። ልጆቹ በቁጥር ወደ 170 ይጠጋሉ በዚህ ተገርመን ሳናበቃ ኡስታዙ ቀጠለ ‘እንደሁ በሌቱ ጭለማ ከሩቅ ስለሚመጡ የሚረፍድባቸው ልጆች ስላሉ እንጂ በጥቅሉ 300 ናቸው’ አለን ። ወዲያው የዕለቱ የኘሮግራም ስነስርዓት ተጀመረ ።
ከመስጂዱ ግቢ መሐል ላይ ያለውን የእንጨት ክምር ከበው በጭለማ እየተደነጋገዙ ለቂርኣት የተቀመጡ ህፃናት ድንገት ፀጥታ ወረሳቸው ። አሚራቸው እሣት አንድዶ ክምሩን ለኮሰውና ። ወዲያው ጭለማው በብርሃን ብርዱ በሙቀት ተተካ ። ያኔ ነው ያማረ የቁርኣን ዜማ ከህፃናቱ ጣፋጭ ኣንደበት መንቆርቆር የጀመረው ።
‘ዱካብ’ ይባላል አሉን ። ቂርኣታቸውን እንደጨረሱ ። ዘወትር ከሱብሂ ቡኋላ የእሳቱን ዳር ከበው በቁርኣን አላህን ያወጉታል ። ይሄ ስርኣት ነው የትላንት ህፃናትን አሳድጎ ዛሬ ላይ ለኡስታዝነት ያበቃው ። በአካባቢው ከ30 አመት በላይ የኖረ የቂርኣት ልምድ ነው ። እኛም የቁርኣንን ፍቅር ከጣፋጭ እንቅልፍ አብልጠው ፣ ጀነትን ፍለጋ ከዱንያ ምቾት ርቀው ፣ በቁርኣን እጥረት ዛሬ ድረስ ጣውላ ላይ ቃሉን እየፃፉ የሚያነቡ አስገራሚ የቁርኣን ትውልዶችን ተመለከትን! በታሪካዊው የቤንሻንጉል ሀገር በጀግናው የሸሆጀሌ ምድር ።
በመጨረሻም የኑር የቁርኣን ባንክ ኢስላማዊ ማህበር የጉዞ አባላት ለ300 ተማሪዎች 300 የቁርኣን ኮፒዎችን ሰጥቶ ሲያበቃ መልዕክታቸውን ጠይቆ ነበር ። እነርሱም እንዲህ ይላሉ “እኛ ቤንሻንጉል ጉምዞች ለመላው የኢትዮጵያ ሙስሊም ወንድሞች እንደመሆናችን ሙስሊሙ ወገን ህመማችን ሊሰማው ችግራችን ሊያሳስበቸው ግድ ይላል! እስከዛሬ ማንም ጎብኝቶን አያውቅም! እኛ ግን እንናፍቃለን! የሙስሊም ወገኖቻችንን ድጋፍ! እገዛ! አይዟችሁ ባይነትን! ወላሒ ተርበናችኋልና እስቲ እንደሁ ምጡና ዘይሩን’ ይላሉ ።
እኛም እንላለን ። አቅሙ ያላችሁ ወንድም እህቶች በሙሉ እኒህን ወገኖች በአልባሳት ፣ በምግብ ፣ በቁሳቁስ እንዲሁም ውሃ በማስቆፈር አለንላችሁ ትሏቸው ዘንድ ማህበራችን መንገዱን ያመቻቻል ።